በእንባ የተጻፈ መልእክት
በዚያ አንድ ሰው ጳውሎስን በድሎት ነበር፣ አብዛኞቹም ቀጥተውታል። ጳውሎስ አሁን ይበቃል ይላል፦ ኀዘን ሳይውጠው ይቅር በሉት። በእንባ የጻፈውን ደብዳቤና የቀረውን ጉብኝት ያብራራል፤ ሁለቱም ቅዝቃዜ ሳይሆኑ ዳግመኛ ሊያቆስላቸው የማይወድ ፍቅር ናቸው።
2 1ስለዚህ ዳግመኛ በኀዘን ወደ እናንተ ላለመምጣት በልቤ ቈረጥሁ። 2እኔ ባሳዝናችሁ፣ ካሳዘንሁት ሰው በቀር ደስ የሚያሰኘኝ ማን ይቀራል? 3ይህን የጻፍሁት መጥቼ ደስ ሊያሰኙኝ ከሚገባቸው ሰዎች ኀዘን እንዳይደርስብኝ ነው፤ ደስታዬ የሁላችሁም ደስታ እንደ ሆነ በሁላችሁ ላይ ተማምኛለሁና። 4ከብዙ መከራና ከልብ ጭንቅ የተነሣ በብዙ እንባ ጻፍሁላችሁ፤ ይህም ላሳዝናችሁ ሳይሆን ለእናንተ ያለኝን የተትረፈረፈ ፍቅር ላሳያችሁ ነው።
5ማንም ያሳዘነ ቢኖር፣ በመጠኑ ሁላችሁን እንጂ እኔን ብዙ አላሳዘነኝም፤ ይህን የምለው ልከብድበት ስለማልፈልግ ነው።
ይቅር በሉት፣ መልሱትም
6እንደዚህ ላለው ሰው ከአብዛኞቻችሁ የተሰጠው ይህ ቅጣት ይበቃዋል። 7ስለዚህ አሁን በተቃራኒው ከልክ ባለፈ ኀዘን እንዳይዋጥ ይቅር ልትሉትና ልታጽናኑት ይገባል። 8ስለዚህ ፍቅራችሁን ለእርሱ እንደ ገና እንድታረጋግጡ እለምናችኋለሁ። 9በሁሉ ነገር ታዛዦች መሆናችሁን ልፈትናችሁና ላውቅ ይህን ደግሞ ጻፍሁ። 10እናንተ ይቅር የምትሉትን እኔም ይቅር እለዋለሁ። እኔ ይቅር ያልሁት ነገር ቢኖር፣ ስለ እናንተ ብዬ በክርስቶስ ፊት ይቅር ብያለሁ፤ 11ይህም ሰይጣን እንዳያታልለን ነው፤ ተንኰሉን አናጣውምና።
12የክርስቶስን ወንጌል ለመስበክ ወደ ጢሮአዳ በመጣሁ ጊዜ፣ በጌታ አንድ በር ተከፈተልኝ፤ 13ነገር ግን ወንድሜን ቲቶን በዚያ ስላላገኘሁት መንፈሴ ዕረፍት አጣ። ስለዚህ ተሰናብቻቸው ወደ መቄዶንያ ሄድሁ።
14ነገር ግን ሁልጊዜ በክርስቶስ በድል ለሚመራንና በእኛ በኩል እርሱን የማወቅን መዐዛ በየቦታው ለሚያሰራጨው ለአባታችን ምስጋና ይሁን። a a v14 የድል ጒዞ የሮም ድል አድራጊ ጦር ሠራዊት ሰልፍ ነበር፤ አሸናፊው አዛዥ ምርኮኞቹን እየመራ በመንገዱ ላይ ጥሩ መዐዛ ያለውን ዕጣን ያጨስ ነበር፤ ጳውሎስም አባታችን ሕዝቡን በክርስቶስ ድል እየመራ እንደ ሆነ ይስላል። 15እኛ በሚድኑትና በሚጠፉት መካከል ለአባታችን የክርስቶስ መዐዛ ነንና፤ 16ለአንዱ ከሞት ወደ ሞት የሆነ መዐዛ፣ ለሌላው ከሕይወት ወደ ሕይወት የሆነ መዐዛ ነን። ለዚህስ ብቁ የሆነ ማን ነው? 17እኛ እንደ ብዙዎቹ የአባታችንን ቃል የምንሸቅጥ አይደለንም፤ ነገር ግን በቅንነት፣ ከእርሱ እንደ ተላክን፣ በእርሱ ፊት በክርስቶስ እንናገራለን።