አዲስ መዝሙር
መዝሙር።
አስቀድሞ ለተፈጸመ ነገር የቀረበ የድል መዝሙር ነው፤ ይኸውም አብ በገዛ ክንዱ ያገኘውና ለሚመለከቱት አሕዛብ በግልጥ ያሳየው ማዳን ሲሆን፣ በእርሱም ለእስራኤል ታማኝነቱን ጠበቀ። ከዚያም የዜማ መሣሪያዎች ይጀምራሉ፤ በቅንነት ሊፈርድ ስለሚመጣ ወንዞች ያጨበጭባሉ፣ ኮረብቶችም ይዘምራሉ።
98 1ለአባታችን አዲስ መዝሙር ዘምሩ፤ ድንቅ ነገሮችን አድርጓልና፤ ቀኝ እጁና ቅዱስ ክንዱ ድነትን አስገኝተውለታል። 2አባታችን ድነቱን አስታውቋል፤ ጽድቁን በአሕዛብ ፊት ገልጧል። 3ለእስራኤል ቤት ያለውን ምሕረቱንና ታማኝነቱን አስታውሷል፤ የምድር ዳርቻዎች ሁሉ የአባታችንን ድነት አይተዋል።
4ምድር ሁሉ፣ ለአባታችን በደስታ ጩኹ፤ በደስታ እልል እያላችሁ ዘምሩ፤ አመስግኑ። 5ለአባታችን በበገና ዘምሩ፤ በበገናና በዜማ ድምፅ ዘምሩ። 6በመለከትና በቀንደ መለከት ድምፅ፣ በንጉሡ በአባታችን ፊት በደስታ ጩኹ።
7ባሕርና በውስጡ ያለው ሁሉ ይንጐድጐድ፤ ዓለምና በእርሱ የሚኖሩ ሁሉ። 8ወንዞች እጃቸውን ያጨብጭቡ፤ ኮረብቶች በአንድነት በደስታ ይዘምሩ፤ 9በአባታችን ፊት፤ እርሱ ምድርን ሊፈርድ ይመጣልና፤ ዓለምን በጽድቅ ይፈርዳል፤ ሕዝቦችንም በቅንነት።