ልባችሁን ከሐሰተኛ ነቢያት ጠብቁ
ምልክቱ የተፈጸመለት ነቢይ እንኳ ሌሎችን አማልክት ተከተሉ ቢል ይጣላል፤ አብ በፍጹም ልባችሁ ትወዱት እንደ ሆነ እየፈተናችሁ ነው። ይህ ለተወደደ ወንድም፣ ሚስት ወይም ወዳጅ፣ ለአንዲት ከተማ ሁሉ ደግሞ ይሠራል፤ ይህ በእስራኤል ላይ የሚደርስ እጅግ የከፋው አደጋ ነው።
13 1ነቢይ ወይም ሕልም አላሚ በመካከላችሁ ቢነሣ ምልክት ወይም ድንቅ ቢሰጣችሁ፣ 2የተናገረውም ምልክት ወይም ድንቅ ቢፈጸም፣ ‘ያላወቃችኋቸውን ሌሎች አማልክት እንከተል፤ እናገልግላቸውም’ ቢል፣ 3የዚያን ነቢይ ወይም ሕልም አላሚ ቃል አትስሙ። አባታችሁን በፍጹም ልባችሁና በፍጹም ነፍሳችሁ ትወዱ እንደ ሆነ ለማወቅ አባታችሁ ይፈትናችኋል። 4አባታችሁን ተከተሉ፤ እርሱንም ፍሩ፤ ትእዛዛቱንም ጠብቁ፤ ቃሉንም ታዘዙ፤ አገልግሉት፤ ተጠጋጉት። 5ያ ነቢይ ወይም ሕልም አላሚ ይገደል፤ ከግብፅ ያወጣችሁን ከባርነትም ቤት ያዳናችሁን አባታችሁን በመቃወም ዐመፅን ተናግሯልና፤ አባታችሁ እንድትሄዱበት ካዘዛችሁ መንገድም ሊያስታችሁ ፈልጓል። ስለዚህ ክፋትን ከመካከላችሁ አስወግዱ።
6ወንድምህ፣ የእናትህ ልጅ፣ ወይም ወንድ ልጅህ ወይም ሴት ልጅህ፣ ወይም በብብትህ ያለች ሚስትህ፣ ወይም እንደ ነፍስህ የምትወደው ወዳጅህ በስውር አባብሎ፣ ‘ሄደን ሌሎች አማልክትን እናገልግል’ ቢልህ— አንተና አባቶችህ ያላወቃችኋቸው አማልክት፣ 7በዙሪያህ ካሉ ሕዝቦች አማልክት፣ ቅርብም ሆነ ሩቅ፣ ከምድር ዳር እስከ ዳር ካሉት ሲሆኑ ነው።’ 8አትስማማው፤ ቃሉንም አትስማ፤ አትራራለት፤ አትማረው ወይም አትሰውረው። 9አይሆንም፤ በእርግጥ ትገድለዋለህ፤ እርሱን ለመግደል እጅህ አስቀድማ ትነሣበት፤ ከዚያም የሕዝቡ ሁሉ እጅ ይነሣበት። 10በድንጋይ ወግረህ ግደለው፤ ከግብፅ ከባርነት ቤት ያወጣህን አባትህን ትተህ እንድትመለስ ሊያሳስትህ ፈልጓልና። 11እስራኤልም ሁሉ ሰምተው ይፈራሉ፤ እንደዚህ ያለውንም ክፉ ነገር ዳግመኛ በመካከላችሁ አያደርጉም።
12አባትህ ልትኖርባቸው ከሚሰጥህ ከተሞችህ ስለ አንዱ ሲነገር ብትሰማ፣ 13ከመካከልህ ምናምንቴ ሰዎች ወጥተው፣ ‘ሄደን ያላወቃችኋቸውን ሌሎች አማልክት እናገልግል’ ብለው የከተማቸውን ነዋሪዎች ካሳቱ፣ 14መርምር፤ ጠይቅ፤ በጥንቃቄም አጣራ። ይህ አስጸያፊ ነገር በመካከልህ እንደ ተደረገ እውነት ሆኖ ቢረጋገጥ፣ 15የዚያችን ከተማ ነዋሪዎች በሰይፍ ስለት ፈጽመህ ምታ፤ ከተማይቱን በውስጧ ያለውን ሁሉ ከብቶቿንም በሰይፍ ስለት ፈጽመህ አጥፋት። 16ምርኮዋንም ሁሉ በአደባባይዋ መካከል ሰብስብ፤ ከተማይቱንም ምርኮዋንም ሁሉ ለአባትህ ሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ በእሳት አቃጥል። ለዘላለምም ፍርስራሽ ሆና ትኖራለች፤ ዳግመኛም አትሠራም። 17ለጥፋት ከተለየው ነገር ምንም በእጅህ አይጣበቅ፤ ይህም አባትህ ከጽኑ ቍጣው ተመልሶ ርኅራኄን ይሰጥህ ዘንድ፣ ይምርህ ዘንድ፣ ለአባቶችህ እንደ ማለላቸውም ያበዛህ ዘንድ ነው፤ 18ዛሬ የማዝህን ትእዛዛቱን ሁሉ በመጠበቅ የአባትህን ቃል ብትታዘዝ፣ በአባትህም ፊት መልካም የሆነውን ብታደርግ ነው።