አባት ሆይ፣ ፍረድልኝ
የዳዊት መዝሙር።
ዳዊት ከአታላዮች ጓደኝነትና ጉቦ ከሞላባቸው እጆች ርቆ ስለኖረ፣ እንዲመረመር፣ ልቡና አእምሮው እንዲፈተኑና እንዲነጹ ይለምናል። የሚፈልገው ፍርድ ሳይሆን ስፍራ ነው፤ የአብ ክብር የሚያድርበትን ቤት።
26 1አባቴ ሆይ፣ ፍረድልኝ፤ በቅንነቴ ተመላልሻለሁና፤ በአባቴም ሳልወላውል ታምኛለሁ።
2አባቴ ሆይ፣ መርምረኝ፤ ፈትነኝም፤ ልቤንና አእምሮዬን አንጥር። 3ምሕረትህ በዓይኖቼ ፊት ነውና፤ በታማኝነትህም እመላለሳለሁ።
4ከሐሰተኞች ሰዎች ጋራ አልቀመጥም፤ ከግብዞችም ጋራ አልተባበርም። 5የክፉ አድራጊዎችን ጉባኤ ጠልቻለሁ፤ ከክፉዎችም ጋራ አልቀመጥም። 6እጆቼን በንጽሕና እታጠባለሁ፤ አባቴ ሆይ፣ መሠዊያህንም እዞራለሁ፤ 7ምስጋናዬን በታላቅ ድምፅ እያወጅሁ፣ ድንቅ ሥራዎችህንም ሁሉ እየተናገርሁ።
8አባቴ ሆይ፣ የምትኖርበትን ቤት፣ ክብርህ የሚያድርበትን ስፍራ እወድዳለሁ።
9ነፍሴን ከኀጢአተኞች ጋራ አትጥረግ፤ ሕይወቴንም ከጨካኝ ሰዎች ጋራ፤ 10በእጆቻቸው ክፉ ሴራ አለ፤ ቀኝ እጃቸውም ጉቦ ሞልቶበታል። 11እኔ ግን በቅንነቴ እመላለሳለሁ፤ ተቤዠኝ፤ ማረኝም።
12እግሬ በደልዳላ ስፍራ ቆሟል፤ በታላቁ ጉባኤ አባቴን እባርካለሁ።