ሞዓብና ይሁዳ ወደ ቤት ተጠሩ
ፍርዶቹ ከሞዓብና ከይሁዳ ወደ እስራኤል ራሷ እየከበቡ ይቀርባሉ፤ ክሱም ግልጽ ነው፦ ጻድቁን በብር፣ ችግረኛውን በጫማ መሸጥ፣ ድሆችን መርገጥ፣ ነቢያትን ዝም ማሰኘት። አብ የሰጣቸውን ይዘረዝራል፤ ከዚያም እንደሚያደቅቃቸው ይናገራል።
2 1አባታችን እንዲህ ይላል፤ ስለ ሞዓብ ሦስት ኀጢአት፣ አዎ ስለ አራቱ ፍርዴን አልመልስም፤ የኤዶምን ንጉሥ ዐጥንቶች አቃጥሎ ኖራ አድርጎአልና። 2ስለዚህ በሞዓብ ላይ እሳት እሰዳለሁ፤ የቄርዮትንም ምሽጎች ይበላል፤ ሞዓብ በጩኸትና በመለከት ድምፅ፣ በሁከት መካከል ይሞታል። 3ገዥውን ከመካከልዋ አጠፋለሁ፤ መኳንንቶቿንም ሁሉ ከእርሱ ጋር እገድላለሁ፤ ይላል አባታችን።
4አባታችን እንዲህ ይላል፤ ስለ ይሁዳ ሦስት ኀጢአት፣ አዎ ስለ አራቱ ፍርዴን አልመልስም፤ የአባታችንን ሕግ ናቁ፤ ሥርዐቱንም አልጠበቁም፤ አባቶቻቸው የተከተሉት ያው ውሸት አሳታቸው። 5ስለዚህ በይሁዳ ላይ እሳት እሰዳለሁ፤ የኢየሩሳሌምንም ምሽጎች ይበላል።
የአባታችን ፍርድ በእስራኤል ላይ
6አባታችን እንዲህ ይላል፤ ስለ እስራኤል ሦስት ኀጢአት፣ አዎ ስለ አራቱ ፍርዴን አልመልስም፤ ጻድቁን በብር፣ ችግረኛውንም በአንድ ጥንድ ጫማ ይሸጣሉና። 7የድኾችን ራስ በምድር ትቢያ ላይ ይረግጣሉ፤ የተገፉትንም ከመንገድ ያርቃሉ። ሰውዬውና አባቱ ወደ አንዲት ብላቴና ይገባሉ፤ ቅዱስ ስሜንም ያረክሳሉ። 8በመያዣ በተወሰደ ልብስ ላይ በየመሠዊያው አጠገብ ይተኛሉ፤ የተቀጡትንም ሰዎች ወይን ጠጅ በአምላካቸው ቤት ይጠጣሉ። 9ነገር ግን እንደ ዝግባ ረዥም፣ እንደ ዋርካም ብርቱ የነበረውን አሞራዊ ከፊታቸው ያጠፋሁት እኔ ነኝ፤ ከላይ ፍሬውን፣ ከታችም ሥሩን አጠፋሁ። 10ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ፣ የአሞራዊውንም ምድር ትወርሱ ዘንድ አርባ ዓመት በምድረ በዳ የመራኋችሁ እኔ ነኝ። 11ከወንዶች ልጆቻችሁ አንዳንዶቹን ነቢያት አድርጌ፣ ከጎበዛዝቶቻችሁም አንዳንዶቹን ናዝራውያን አድርጌ አስነሣሁ። የእስራኤል ልጆች ሆይ፤ ይህ እንዲህ አይደለምን? ይላል አባታችን። a a v11 ናዝራውያን ለእግዚአብሔር የተለየ የመወሰን ስእለት ተስለው ከወይን ጠጅ የሚከለከሉና ጠጕራቸውን የማይላጩ እስራኤላውያን ነበሩ (ዘኍልቍ 6ን ተመልከት)። 12እናንተ ግን ናዝራውያኑን ወይን ጠጅ አጠጣችኋቸው፤ ነቢያቱንም፣ “ትንቢት አትናገሩ” ብላችሁ አዘዛችኋቸው። 13እነሆ፤ ነዶ የሞላበት ጋሪ ከበታቹ ያለውን ምድር እንደሚጭን፣ በስፍራችሁ እጫናችኋለሁ። 14ፈጣኑ እንኳ ማምለጫ አያገኝም፤ ብርቱውም ኀይሉን አያጸናም፤ ጦረኛውም ነፍሱን አያድንም። 15ቀስተኛው አይቆምም፤ እግረ ፈጣኑም አያመልጥም፤ ፈረሰኛውም ነፍሱን አያድንም። 16ከጦረኞችም ሁሉ ይበልጥ ደፋሩ በዚያ ቀን ዕራቁቱን ይሸሻል፤ ይላል አባታችን።