አባታችን የተሳሳተውን ንጉሡን ይገሥጻል
ኢዩ የሚመለሰውን ንጉሥ በጥያቄ ይቀበለዋል፦ ኃጢአተኛውን ልትረዳ ይገባሃልን? ኢዮሣፍጥ ሕዝቡን በመዞርና ፈራጆችን በመሾም ይመልሳል፤ ለሰው ሳይሆን ለአብ እንደሚፈርዱ፣ በእርሱም ዘንድ ዓመፃ፣ አድልዎ ወይም መማለጃ እንደሌለ ይነግራቸዋል።
19 1የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤቱ በሰላም ተመለሰ። 2ባለ ራእዩ የሐናኒ ልጅ ዩሁ ንጉሡን ኢዮሣፍጥን አግኝቶ እንዲህ አለው፤ “ክፉዎችን ትረዳና አባታችንን የሚጠሉትን ትወዳለህን? ስለዚህ ከአባታችን ዘንድ ቍጣ በአንተ ላይ መጥቶአል። 3ሆኖም መልካም ነገር በአንተ ተገኝቶአል፤ የአሼራ ዐፀዶችን ከምድሪቱ አስወግደሃል፤ አባታችንንም ለመሻት ልብህን አዘጋጅተሃል።”
4ኢዮሣፍጥ በኢየሩሳሌም ተቀመጠ፤ እንደ ገናም ከቤርሳቤህ ጀምሮ እስከ ኤፍሬም ተራራማ አገር ድረስ በሕዝቡ መካከል ወጣ፤ ወደ አባታችን ወደ አባቶቻቸው አምላክም መለሳቸው። 5በምድሪቱ ውስጥ በይሁዳ በተመሸጉ ከተሞች ሁሉ ከተማ በከተማ ዳኞችን ሾመ። 6ዳኞቹንም እንዲህ አላቸው፤ “የምታደርጉትን ተመልከቱ፤ ለሰው ሳይሆን ለአባታችን ትፈርዳላችሁና፤ በምትፈርዱበትም ጕዳይ ሁሉ እርሱ ከእናንተ ጋራ ነው። 7አሁንም የአባታችን ፍርሃት በእናንተ ላይ ይሁን፤ ተጠንቅቃችሁ አድርጉ፤ በአባታችን ዘንድ ዐመፅም ሆነ አድልዎ ወይም ጕቦ የለምና።”
8ኢዮሣፍጥ ደግሞ የአባታችንን ፍርድ ይፈጽሙ ዘንድና ክርክሮችን ይፈቱ ዘንድ ከሌዋውያን፣ ከካህናትና ከእስራኤል የአባቶች ቤቶች አለቆች አንዳንዶችን በኢየሩሳሌም ሾመ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም ተመለሱ። 9አዘዛቸውም፤ “አባታችንን በመፍራት፣ በታማኝነትና በፍጹም ልባችሁ እንዲህ አድርጉ። 10በከተሞቻቸው የሚኖሩ ወንድሞቻችሁ ስለ ደም ማፍሰስ ወይም ስለ ሕግና ትእዛዝ፣ ስለ ሥርዐትና ፍርድ ክርክር ባመጡላችሁ ጊዜ ሁሉ፣ በአባታችን ፊት በደለኞች ሆነው በእናንተና በወንድሞቻችሁ ላይ ቍጣ እንዳያመጡ አስጠንቅቋቸው፤ እንዲህ ብታደርጉ በደለኞች አትሆኑም። 11አሁንም ሊቀ ካህናቱ አማርያ በአባታችን ነገር ሁሉ ላያችሁ ነው፤ የእስማኤል ልጅ ዘባድያም የይሁዳ ነገድ አለቃ በንጉሡ ነገር ሁሉ ላያችሁ ነው። ሌዋውያኑም በፊታችሁ ሹማምት ሆነው ያገለግላሉ። በርቱ፤ አድርጉም፤ አባታችንም መልካም ከሚያደርጉት ጋራ ይሁን።”