አባታችን ለካህናቱ ያስፈልጋቸውን ያሟላል
ካህናቱ ርስት ስለሌላቸው ከመሥዋዕቱ ይኖራሉ። የአሕዛብ ሟርት፣ መተትና ሙታንን መጠየቅ ፈጽሞ ተከልክሏል። ይልቁንም አብ ከወንድሞቻቸው መካከል እንደ ሙሴ ያለ ነቢይ ያስነሣል። ነቢዩ የተላከ መሆኑ የሚፈተነው ቃሉ በመፈጸሙ ነው።
18 1ሌዋውያን ካህናት፣ ማለትም መላው የሌዊ ነገድ፣ ከእስራኤል ጋራ ድርሻም ሆነ ርስት የላቸውም፤ የአባታችን ርስት የሆነውን፣ ለእርሱ የሚቀርበውን መሥዋዕት ይበላሉ። 2በወንድሞቻቸው መካከል ርስት አይኖራቸውም፤ እርሱ ተስፋ እንደ ሰጣቸው፣ አባታችን ራሱ ርስታቸው ነው። 3ከሕዝቡ ለካህናቱ የሚገባቸው ድርሻ ይህ ነው፤ በሬ ወይም በግ የሚሠዉ ሰዎች ለካህኑ ትከሻውን፣ ሁለቱንም ጕንጭ፣ ሆዱንም ይስጡ። 4ከእህልህ፣ ከወይን ጠጅህና ከዘይትህ በኵራት፣ እንዲሁም ከበጎችህ መጀመሪያ ጠጕር ስጠው። 5አባትህ እርሱና ልጆቹ በአባታችን ስም ቆመው ዘወትር እንዲያገለግሉ ከነገዶችህ ሁሉ መርጦታልና።
6አንድ ሌዋዊ በእስራኤል ውስጥ ከሚኖርባት ከማናቸውም ከተማህ ወጥቶ፣ በፈለገ ጊዜ ሁሉ አባታችን ወደ ሚመርጠው ስፍራ ቢመጣ፣ 7በዚያ በአባታችን ፊት እንደሚቆሙት እንደ ሌሎች ባልንጀሮቹ ሌዋውያን ሁሉ፣ በአባታችን ስም ያገልግል። 8ከቤተሰቡ ንብረት ሽያጭ ከሚያገኘው ሌላ፣ እኩል ድርሻ ይብላ።
አብ የጥንቈላ ድርጊቶችን ይከለክላል
9አባትህ ወደ ሚሰጥህ ምድር በገባህ ጊዜ፣ የእነዚያን አሕዛብ አስጸያፊ ድርጊቶች ልትኰርጅ አትማር። 10ከእናንተ መካከል ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን በእሳት የሚሠዋ፣ ሟርተኛ፣ ኮከብ ቈጣሪ፣ ምልክቶችን የሚመረምር ወይም አስማተኛ ማንም አይገኝ፤ 11መተት የሚያደርግ፣ መናፍስት ጠሪ፣ መናፍስትን የሚያማክር ወይም ሙታንን የሚጠይቅ ማንም አይገኝ። 12ይህን የሚያደርግ ሁሉ በአባታችን ዘንድ አስጸያፊ ነውና፤ በእነዚህ አስጸያፊ ድርጊቶች የተነሣ፣ አባትህ ከፊትህ ያስወጣቸዋል። 13በአባትህ ፊት ነውር የሌለብህ ሁን። 14ልትወርሳቸው ያሉት እነዚህ አሕዛብ ኮከብ ቈጣሪዎችንና ሟርተኞችን ይሰማሉ፤ አባትህ ግን ይህን አልፈቀደልህም።
አብ ነቢይ ይልካል
15አባትህ ከመካከልህ፣ ከወንድሞችህ፣ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣልሃል፤ እርሱን ስማ። a a v15 ጴጥሮስና እስጢፋኖስ ኢየሱስን፣ አባታችን ሊያስነሣው ተስፋ የሰጠውን ነቢይ አድርገው ይጠሩታል፤ እርሱም እስራኤላዊ ሁሉ ሊሰማው የሚገባው ነው (የሐዋርያት ሥራ 3፥22-23፤ የሐዋርያት ሥራ 7፥37)። 16በማኅበሩ ቀን በኮሬብ ከአባትህ የለመንኸው ይህ ነው፤ “የአባታችንን ድምፅ ዳግመኛ እንዳልሰማ፣ ይህንም ታላቅ እሳት ከእንግዲህ እንዳላይ፤ አለዚያ እሞታለሁ።”
17አባታችንም እንዲህ አለኝ፤ “የተናገሩት ልክ ነው። 18ከወንድሞቻቸው መካከል እንደ አንተ ያለ ነቢይ አስነሣላቸዋለሁ፤ ቃሌንም በአፉ አኖራለሁ፤ የማዝዘውንም ሁሉ ይነግራቸዋል። 19በስሜ የሚናገረውን ቃሌን የማይሰማውን ሰው ሁሉ፣ እኔ ራሴ እጠይቀዋለሁ። 20ያላዘዝሁትን ቃል በስሜ ለመናገር የሚደፍር፣ ወይም በሌሎች አማልክት ስም የሚናገር ነቢይ ግን፣ ያ ነቢይ ይሙት።”
21በልብህም፣ “አባታችን ያልተናገረውን ቃል እንዴት እናውቃለን?” ብትል፣ 22አንድ ነቢይ በአባታችን ስም ተናግሮ ነገሩ ባይፈጸም ወይም እውነት ባይሆን፣ ያን ቃል አባታችን አልተናገረውም፤ ነቢዩ በድፍረት ተናግሮታል፤ አትፍራው።