ለአባታችን ደጆች የተሾሙ የደጅ ጠባቂዎች
በር ጠባቂዎች በዕጣ ለአብ ቤት ለእያንዳንዱ አቅጣጫ ይመደባሉ፤ ብርቱዎቹ የዖቤድ ኤዶም ልጆችም ለሥራው ብቁ ሰዎች ተብለው ይቈጠራሉ። ሌሎች የተቀደሰውን ሀብትና የጦርነት ምርኮ በኀላፊነት ይይዛሉ፤ አንዳንዶቹም አለቆችና ፈራጆች ሆነው ይላካሉ።
26 1የደጅ ጠባቂዎች ክፍሎች ይህ ነበር፦ ከቆራሆች ወገን፣ ከአሳፍ ልጆች የሆነው የቆሬ ልጅ ሜሰሌምያ። 2ሜሰሌምያ ልጆች ነበሩት፤ በኵር ዘካርያስ፣ ሁለተኛው ይድያኤል፣ ሦስተኛው ዘባድያ፣ አራተኛው ያትኒኤል፣ 3አምስተኛው ዔላም፣ ስድስተኛው ይሆሐናን፣ ሰባተኛው ኤልዩሆዔናይ ነበሩ። 4ዖቤድ ኤዶምም ልጆች ነበሩት፤ በኵር ሸማያ፣ ሁለተኛው ይሆዛባድ፣ ሦስተኛው ዮአሕ፣ አራተኛው ሳካር፣ አምስተኛው ናትናኤል፣ 5ስድስተኛው ዓሚኤል፣ ሰባተኛው ይሳኮር፣ ስምንተኛው ጴዩልታይ ነበሩ፤ አባታችን ባርኮት ነበርና። 6ልጁ ሸማያም በአባታቸው ቤተ ሰብ ላይ የተሾሙ ልጆች ነበሩት፤ እነርሱ ኀያላን ጀግኖች ነበሩና። 7የሸማያ ልጆች፦ ዖትኒ፣ ሬፋኤል፣ ዖቤድና ኤልዛባድ ነበሩ፤ ወንድሞቻቸው ኤሊሁና ሰማክያም የተዋጣላቸው ሰዎች ነበሩ። 8እነዚህ ሁሉ ከዖቤድ ኤዶም ልጆች ነበሩ፤ እነርሱ፣ ልጆቻቸውና ወንድሞቻቸው ለሥራው የበረቱና የተዋጣላቸው ነበሩ፤ ከዖቤድ ኤዶም ስድሳ ሁለት ነበሩ። 9ሜሰሌምያ የተዋጣላቸው ልጆችና ወንድሞች ነበሩት፤ በጠቅላላው ዐሥራ ስምንት ነበሩ። 10ከምራሪ ልጆች የሆነው ሖሳም ልጆች ነበሩት፤ አለቃው ሺምሪ ነበር፤ በኵር ባይሆንም አባቱ አለቃ አደረገው። 11ሁለተኛው ኬልቅያስ፣ ሦስተኛው ጠበልያ፣ አራተኛው ዘካርያስ ነበር፤ የሖሳ ልጆችና ወንድሞች በጠቅላላው ዐሥራ ሦስት ነበሩ።
12እነዚህ በአለቆች የተመደቡ የደጅ ጠባቂዎች ክፍሎች እንደ ወንድሞቻቸው በአባታችን ቤት ያገለግሉ ነበር። 13ታናሽም ታላቅም እንደ ቤተ ሰባቸው ለእያንዳንዱ ደጅ ዕጣ ተጣጣሉ። 14የምሥራቅ ዕጣ ለሰሌምያ ወጣ። ጠቢብ አማካሪ ለሆነው ለልጁ ለዘካርያስም ዕጣ ተጣጣሉ፤ ዕጣውም ወደ ሰሜን ወጣ። 15ለዖቤድ ኤዶም የደቡብ ዕጣ ወጣ፤ ለልጆቹም መዛግብት ቤት ወጣ። 16ለሱፊምና ለሖሳ የምዕራብ ዕጣ ወጣ፤ ወደ ላይ በሚወጣው መንገድ ላይ ካለው ከሰሌከት ደጅ ጋራ ነበር፤ ጠባቂም ለጠባቂ ትይዩ ነበር። 17በምሥራቅ ስድስት ሌዋውያን ይቆሙ ነበር፤ በሰሜን በየዕለቱ አራት፣ በደቡብ በየዕለቱ አራት፣ በመዛግብት ቤትም ሁለት ሁለት ሆነው ይቆሙ ነበር። 18በምዕራብ በኩል ባለው ዐደባባይ፦ በመንገዱ አራት፣ በዐደባባዩም ሁለት ነበሩ። 19ከቆራሆችና ከምራራውያን ወገን የደጅ ጠባቂዎች ክፍሎች እነዚህ ነበሩ።
የአባታችን ገንዘብ ያዦች፣ ሹማምትና ዳኞች
20ሌዋዊው አኪያም የአባታችንን ቤት መዛግብትና የተቀደሱትን ስጦታዎች መዛግብት ይቆጣጠር ነበር። 21የሊዳን ልጆች፣ ለሊዳን የሆኑ ጌራሳውያን፣ የጌራሳዊው የሊዳን የቤተ ሰብ አለቆች፦ ይሒኤሊ ነበር። 22የይሒኤሊ ልጆች ዜታምና ወንድሙ ኢዮኤል የአባታችንን ቤት መዛግብት ይቆጣጠሩ ነበር። 23ከዓምራማውያን፣ ከይስዓራውያን፣ ከኬብሮናውያንና ከዑዝኤላውያን ወገን፦ 24የሙሴ ልጅ የሆነው የጌርሶም ልጅ ሸቡኤል በመዛግብቱ ላይ ዋና ኀላፊ ነበር። 25በኤሊዔዘር በኩል ዘመዶቹ፦ ልጁ ረአብያ፣ የእርሱም ልጅ ይሻያ፣ የእርሱም ልጅ ዮራም፣ የእርሱም ልጅ ዚክሪ፣ የእርሱም ልጅ ሸሎሚት ነበሩ። 26ሸሎሚትና ወንድሞቹ ንጉሥ ዳዊት፣ የቤተ ሰብ አለቆች፣ የሺህ አለቆችና የመቶ አለቆች፣ የሰራዊትም አዛዦች የቀደሷቸውን የስጦታ መዛግብት ሁሉ ይቆጣጠሩ ነበር። 27በጦርነት ከተገኘው ምርኮ ውስጥ የአባታችንን ቤት ለመጠገን ስጦታ ቀደሱ። 28ባለ ራእዩ ሳሙኤል፣ የቂስ ልጅ ሳኦል፣ የኔር ልጅ አበኔር፣ የጽሩያም ልጅ ኢዮአብ የቀደሱትን ሁሉ፣ የተቀደሰውን ነገር ሁሉ ሸሎሚትና ወንድሞቹ ይቆጣጠሩ ነበር።
29ከይስዓራውያን ወገን ክናንያና ልጆቹ የእስራኤልን የውጭ ጒዳዮች እንደ ሹማምትና እንደ ዳኞች ሆነው ያስተዳድሩ ነበር። 30ከኬብሮናውያን ወገን ሐሻብያና ዘመዶቹ፣ ዐንድ ሺህ ሰባት መቶ የተዋጣላቸው ሰዎች፣ ለአባታችን ሥራ ሁሉና ለንጉሡ አገልግሎት ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ያለውን እስራኤልን ይቆጣጠሩ ነበር። 31ከኬብሮናውያን መካከል እንደ ቤተ ሰባቸው የትውልድ መዝገብ ይሪያ አለቃ ነበር። በዳዊት በአርባኛው ዓመት ፍለጋ ተደርጎ በገለዓድ ባለው በያዔዜር በመካከላቸው የተዋጣላቸው ሰዎች ተገኙ። 32የይሪያ ዘመዶች ሁለት ሺህ ሰባት መቶ የተዋጣላቸው ሰዎች፣ የቤተ ሰብ አለቆች ነበሩ። ንጉሥ ዳዊትም ለአባታችንና ለንጉሡ ጒዳይ ሁሉ በሮቤላውያን፣ በጋዳውያንና በምናሴ ነገድ እኩሌታ ላይ ሾማቸው።