ዳዊት ሌዋውያንን ለቤቱ ያደራጃቸዋል
ዳዊት አርጅቶ መንግሥቱን ለሰሎሞን ሲያስረክብ፣ ከስፍራው ለማይንቀሳቀስ ቤተ መቅደስ ሌዋውያንን እንደ ገና ያደራጃል። ማደሪያውን ድንኳን የሚሸከም ማንም ስለሌለ ሥራው በአዲስ መልክ ይገለጻል፤ አደባባዮች፣ ዕቃ ቤቶች፣ እንጀራ፣ መስፈሪያዎች፣ እንዲሁም በየማለዳውና በየማታው ቆሞ አብን ማመስገን።
23 1ዳዊት ሸምግሎ ዕድሜው በገፋ ጊዜ፣ ልጁን ሰሎሞንን በእስራኤል ላይ አነገሠው። 2የእስራኤልን መሪዎች ሁሉ ከካህናትና ከሌዋውያን ጋራ አንድ ላይ ሰበሰበ። 3ዕድሜያቸው ሠላሳ ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሌዋውያን ተቈጠሩ፤ ጠቅላላ ቍጥራቸውም ሠላሳ ስምንት ሺህ ነበር። 4ከእነዚህም ውስጥ ሃያ አራት ሺህ የአባታችንን ቤት ሥራ እንዲቈጣጠሩ ተመደቡ፤ ስድስት ሺህ ደግሞ ሹማምትና ዳኞች ነበሩ። 5አራት ሺህ በረኞች ነበሩ፤ አራት ሺህም ዳዊት ለምስጋና በሠራቸው የሙዚቃ መሣሪያዎች አባታችንን አመሰገኑ።
6ዳዊትም እንደ ሌዊ ልጆች፣ እንደ ጌድሶን፣ ቀዓትና ሜራሪ ከፋፍሎ በየክፍሉ መደባቸው።
የጌድሶን ጎሳዎች
7ከጌድሶናውያን፦ ለዓዳንና ሳሚ። 8የለዓዳን ልጆች፦ አለቃው ይሒኤል፣ ቀጥሎም ዜታምና ኢዮኤል፣ በድምሩ ሦስት። 9የሳሚ ልጆች፦ ሰሎሞት፣ ሐዚኤልና ሐራን፣ ሦስት። እነዚህ የለዓዳን የቤተ ሰብ አለቆች ነበሩ። 10የሳሚም ልጆች፦ ያሃት፣ ዚና፣ ይዐውስና ብሪዓ። እነዚህ አራቱ የሳሚ ልጆች ነበሩ። 11ያሃት አለቃ፣ ዚዛ ሁለተኛ ነበር፤ ይዐውስና ብሪዓ ጥቂት ልጆች ስለነበሯቸው እንደ አንድ ቤተ ሰብ፣ እንደ አንድ ምድብ አብረው ተቈጠሩ።
የቀዓት ጎሳዎች
12የቀዓት ልጆች፦ አምራም፣ ይስሃር፣ ኬብሮንና ዑዝኤል፣ በድምሩ አራት። 13የአምራም ልጆች፦ አሮንና ሙሴ። አሮን እርሱና ልጆቹ ለዘላለም እጅግ ቅዱስ የሆኑትን ነገሮች እንዲቀድሱ፣ በአባታችን ፊት መሥዋዕት እንዲያቀርቡ፣ እንዲያገለግሉትና በስሙ ለዘላለም እንዲባርኩ ተለየ። 14ሙሴ ግን የአባታችን ሰው ነበር፤ ልጆቹም በሌዊ ነገድ ተቈጠሩ። 15የሙሴ ልጆች፦ ጌርሾምና ኤሊኤዘር። 16የጌርሾም ልጆች፦ አለቃው ሻቡኤል። 17የኤሊኤዘር ልጆች፦ አለቃው ርህብያ። ኤሊኤዘር ሌላ ልጅ አልነበረውም፤ የርህብያ ልጆች ግን እጅግ ብዙ ነበሩ። 18የይስሃር ልጆች፦ አለቃው ሰሎሚት። 19የኬብሮን ልጆች፦ አለቃው ይሪያ፣ ሁለተኛው አማርያ፣ ሦስተኛው ያሃዝኤል፣ አራተኛውም ይቀምዓም። 20የዑዝኤል ልጆች፦ አለቃው ሚካና ሁለተኛው ይሺያ።
የሜራሪ ጎሳዎች
21የሜራሪ ልጆች፦ መሐሊና ሙሢ። የመሐሊ ልጆች፦ አልዓዛርና ቂስ። 22አልዓዛር ወንዶች ልጆች ሳይኖሩት፣ ሴቶች ልጆች ብቻ ትቶ ሞተ፤ ስለዚህ ዘመዶቻቸው የሆኑት የቂስ ልጆች አገቧቸው። 23የሙሢ ልጆች፦ መሐሊ፣ ዔድርና ይሪሞት፣ በድምሩ ሦስት።
24እነዚህ በቤተ ሰባቸው የተመደቡ የሌዊ ልጆች፣ በስማቸው የተመዘገቡ የቤተ ሰብ አለቆች ነበሩ፤ እነርሱም ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከዚያ በላይ ሆነው በአባታችን ቤት ያገለገሉ ናቸው። 25ዳዊት እንዲህ ብሎ ነበርና፤ “የእስራኤል አምላክ አባታችን ለሕዝቡ ዕረፍት ሰጥቷል፤ በኢየሩሳሌምም ለዘላለም ይኖራል። 26ስለዚህ ሌዋውያን ድንኳኑንም ሆነ የአገልግሎት ዕቃዎቹን ሁሉ ከእንግዲህ አይሸከሙም።” 27በዳዊት በእነዚህ የመጨረሻ ትእዛዛት መሠረት ሌዋውያን ከሃያ ዓመትና ከዚያ በላይ ሆነው ተቈጠሩ። 28ተግባራቸውም የአባታችንን ቤት በማገልገል የአሮንን ልጆች መርዳት ነበር፤ ይኸውም አደባባዮቹንና ክፍሎቹን መንከባከብ፣ ቅዱሳን ነገሮችን ሁሉ ማንጻትና በአባታችን ቤት ያለውን ማንኛውንም ሥራ መሥራት ነበር። 29የገጸ ኅብስቱን፣ ለእህል መባ የሚሆነውን በጎ ዱቄት፣ ያለ እርሾ የተሠራውን ቂጣ፣ መጋገርንና ማቡኰስን እንዲሁም የብዛትና የመጠን ልኬቶችን ሁሉ ይጠባበቁ ነበር። 30በየማለዳውም አባታችንን ለማመስገንና ለማወደስ ይቆሙ ነበር፤ እንዲሁም በማታ፣ 31በሰንበት፣ በወር መባቻና በተወሰኑ በዓላት ለአባታችን በሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ሁሉ ላይ፣ በሚፈለገው ቍጥር መሠረት፣ ዘወትር በአባታችን ፊት ያገለግሉ ነበር። a a v31 የወር መባቻ በእያንዳንዱ አዲስ የዕብራውያን ወር መጀመሪያ ላይ የሚከበር ወርሃዊ በዓል ነበር። 32የመገናኛውን ድንኳን አደራ፣ የመቅደሱን አደራ፣ እንዲሁም የወንድሞቻቸውን የአሮንን ልጆች አደራ በአባታችን ቤት አገልግሎት ይጠብቁ ነበር።